ዉሃን አዘውትሮ መጠጣት የሚሰጠው ጥቅም

 

አንድ ሰዉ በቀን የሚያስፈልገዉ የፈሳሽ መጠን ይህ ነው ብሎ እቅጩን ለመናገር እስከአሁን ስምምነት ላይ ያልተደረሰ ቢሆንም የሚስፈልገዉ የፈሳሽ መጠን በተለያዩ ነገሮች ይወሰናል፡፡ እነዚህም የግለሰቡ ጤንነት፣ የእንቅስቃሴ መጠን፣ እድሜ፣ የአየር ፀባይ(የሚኖርበት ስፍራ)፣ ምን ያህል ዉሃ በቡና፣ በሻይ፣ በጅዉስና በመሳሰሉት መልክ እንደሚወስድና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡ እንደሚያዉቁት በየቀኑ ዉሃ ከሰዉነትዎ በትንፋሽ፣ በላቦት፣ በሽንትና በሰገራ ዉስጥ ይወጣል፡፡ ሰዉነትዎ በአግባቡ እንዲሰራ ከሰዉነትዎ የወጣዉን ፈሳሽ መልሰዉ ለመተካት ዉሀን ጨምሮ ዉሀን የያዙ ፈሳሾችን መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም አንድ ጤነኛ ሰዉ በቀን መዉሰድ የሚገባዉ የዉሀ መጠን ለወንዶች እስከ 3 ሊትር ሲሆን ለሴቶች እስከ 2.2 ሊትር መዉሰድ ይመከራል፡፡

 

ዉሃን በብዛት መጠጣት ለምን ያስፈልጋል?


1.የሰዉነትን የፈሳሽ መጠን ለማመጣጠን፡-

60 ከመቶ የሚሆነዉን ሰዉነታችንን ክፍል የተያዘዉ በዉሃ ነዉ፡፡ የሰዉነት ፈሳሽ ለምግብ መፈጨት፣ለምግብ መመጠጥና ወደተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች መዳረስ፣ ምራቅን ለመስራት፣ንጥረነገሮችን ለሰዉነታችን ለማዳረስ/ለማሰራጨትና የሰዉነትን ሙቀት ለመቆጣጠር ያገለግላል/ይጠቅማል፡፡
አልኮሆል የአእምሮንና የኩላሊትን ግንኙነት ስለሚያዉክና ብዙ ፈሳሽ ከሰዉነታችን እንዲወጣ ስለሚያደርግ ለድርቀት ያጋልጠናል፡፡ ስለሆነም አልኮል ከምንወስደዉ ፈሰሽ ዉስጥ አይመደብም፡፡

 

2. የሰውነት ክብደት መጠንን ለመቀነስ መርዳት፡-

ከፍ ያለ የካሎሪ መጠን ካላቸዉ እንደ ኮካ ያሉ ፈሳሾች ይልቅ ንፁህ ዉሃ መዉሰድ የሰዉነትን ክብደት ለመቆጣጠር/ለመቀነስ ያግዛሉ፡፡ በተጨማሪም ብዙ ፈሳሽነት ያላቸዉ ምግቦች ከፍ ያለ መጠን (volume) ስላላቸዉ፣ በቀላሉ የጥጋብ ስሜት እንዲመጣና ቀስ ብለዉ ስለሚመጠጡ ለክብደት ቁጥጥር ያገለግላሉ፡፡ ብዙ ፈሳሽነት ካላቸዉ ምግቦች ዉስጥ አትክልት፣ ፍራፍሬና ሾርባ ይጠቀሳሉ፡፡


3. ተጨማሪ ሀይልና ጉልበት ለጡንቻዎቻችን ለመስጠት ፡-

የፈሳሽንና ንጥረነገሮችን (ኤሌክትሮላይት) ምጣኔን የማይጠብቁ/ የማይቆጣጠሩ የሰዉነታችን ሴሎች ይሟሽሻሉ፤ ይህ ለጡንቻ መዛል(fatigue) ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ የሰዉነታችን ጡንቻ ሴሎች በቂ ፈሳሽ ካላገኙ/ከሌላቸዉ በትክክል አይሰሩም፤ይህ በመሆኑም እንቅስቃሴዎችን መተግበር ያዳግተናል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግዎ በፊት፣ በሚያደርጉበት ወቅትና ካደረጉ በኃላ በላብ መልክ የሚወጣዉን ፈሳሽ ለመተካት በቂ ፈሳሽ መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡


4. ዉሃ የሰዉነት ቆዳዎ ጥሩ እንዲሆን/እንዲጠራ/እንዲለሰልስ ያግዛል፡-

የሰዉነታችን ቆዳ ብዙ ዉሃ ያለዉ ሲሆን ከሰዉነታችን ዉስጥ ፈሳሽ ከመጠን በላይ እንዳይወጣ ለመከላከል ያገለግላል፡፡ በቂ ፈሳሽ ካልወሰድን ቆዳችን እንዲደርቅና እንዲሸበሸብ የሚያደርግ ሲሆን ይህን ለመከላከል በቂ ፈሳሽ መዉሰድ ይገባናል፡፡ በተጨማሪም ሞይስቸራይዘሮች እርትበት/ፈሳሽ በቆዳችን በኩል እንዳይወጣና ታምቆ እንዲቀር ስለሚያደርጉ የሰዉነት ቆዳ ልስላሴዉን እንዲጠብቅ ይረዱታል፡፡


5. ዉሃ ለኩላሊት የፍሳሽ ማጣራት እና ማስወገድ አቅምን ይጨምራ፡-

የሰዉነት ፈሳሾች ቆሻሻን ወደ ሰዉነት ሴሎች ዉስጥና ዉጪ ለማጓጓዝ ያገለግላሉ፡፡ ለሰዉነታችን ሴሎች መርዛማ ከሆኑት ዉስጥ እንደ ዩሪያ ያሉ ኬሚካሎችን ከሰዉነት በኩላሊት በኩል ለማስወገድ የሚቻለዉ በየቀኑ በቂ ፈሳሽ መዉሰድ ሰንችል ነዉ፡፡ በቂ ፈሳሽ ከወሰድን ሽንታችን በደንብ ይወጣል፣ ነጣ ያለ መልክ እንዲኖረዉና ሽታ እንዳይኖረዉ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሰዉነታችን በቂ ፈሳሽ ካላገኘ የሽንት መጠን እንዲቀንስና እንዲወፍር ያደርጋል፣መልኩ እንዲለወጥና ሽታ እንዲኖረዉ ያደርጋል:: ምክንያቱም ኩላሊት ብዙ ፈሳሽ እንዳይወጣ ስለምትከለክል፡፡


6. ዉሃ የአንጀት ስርዓት በትክክል እንዲሰራ ያደርጋል፡-

በቂ ፈሳሽ መዉሰድ ድርቀትን ይከላከላል፡፡ በቂ ፈሳሽ የማይወስዱ ከሆነ ትልቁ እንጀት ፈሳሽ ወደ ሰዉነታችን መጦ በመመለስ የሰዉነታችንን የፈሳሽ ምጣኔ የሚጠብቅ ሲሆን የኸን በሚያደርግበት ወቅት ድርቀት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ በቂ ፈሳሽ መዉሰድና ቃጫነት(ፋይበርናት) ያለዉ ምግብ መመገብ የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡


በተጨማሪም ዉሃ


• ለመነቃቃት እና የምንሰራው ስራ ላይ የበለጠ ትኩረት ለማድረግ ይረዳል፡፡
• ከልክ ያለፈ መጠጥ በተጠጣበት ግዜ የሃንግኦቨር ስሜትን ይቀንሳል፡፡
• በጡንቻ እና በመገጣጠሚያ ላይ የሚከሰቱ ህመሞችን ይከላከላል፡፡
• የሠውነት የሙቀት መጠንን ለመቆጣጠር ይጠቅማል እንዲሁም
• መጥፎ የአፍ ጠረንን ይከላል፡፡

Recent Posts

Comments

comments