ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብል (Post Pill)

ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች ከወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ዉስጥ የሚመደቡ ሲሆን አገልግሎታቸዉ አንዲት ሴት በድንገት ያለመከላከያ የግብረስጋ ግንኙነት ካደረገች ወይም እየወሰደች ያለዉ የወሊድ መከላከያ ዘዴ እየሰራ ካልሆነ የሚወሰድ ነዉ፡፡
ስለሆነም ይህ የወሊድ መከላከያ አንክብል እንደዋነኛ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ሳይሆን እንደመጠባበቂያ ለድንገተኛ ጊዜ ብቻ/ for backup contraception only/ የሚገለግል ነዉ፡፡ ፐላን ቢ ዋን ስቴፕ የሚባለዉ ድንገተኛ ወሊድ መከላከያ እንክብል ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊገዛ የሚችል ነዉ፡፡
ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብል የተረገዘ እርግዝናን አያቋርጥም፡፡ ነገር ግን እንደወሰዱበት የወር አበባ ዑደት ወቅት ከሚከተሉት መንገድ በአንዱ እርግዝና እንዳይፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡ የእንቁላልን ከአብራኳ አኩርቶ መዉጣትን የመከላከል/የማዘግየት፣የወንድና የሴት የዘር ፍሬዎች እንዳይገናኙ መከላከል አሊያም ቢገናኙም የማህፀን ግድግዳ ላይ እንዳይጣበቁ መከላከል ናቸዉ፡፡

ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች ድንገተኛ የሆነና ያለምንም ጥንቃቄ ከተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት በኃላ የሚከሰትን እርግዝና የመከላከል ብቃት አላቸዉ፡፡ ነገር ግን ከሌሎቹ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ጋር ሲነፃፀሩ የመከላከል ብቃታቸዉ ስለሚያንስ በተደጋጋሚና በመደበኛነት መዉሰድ አይመከርም፡፡ እንዲያዉም ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን በትክክልም ተጠቅመዉ እረግዝናን ሳይከላከሉ ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የአባለዘር በሽታዎችን ሊከላከሉ አይችሉም፡፡

ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን ነፍሰጡር መሆንዎትን ካወቁ እንዳይወስዱ ይመከራሉ፡፡

የድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች የጎንዮሽ ጉዳቶች መድሃኒቶቹን ከወሰዱ በኃላ ለተወሰኑ ቀናቶች ሊቀጥሉ የምችል ሲሆን እነርሱም:

• ማቅለሽለሽ/ ማስታወክ
• መደበት
• የድካም ስሜት/መደካከም
• የራስ ምታት
• የጡት ህመም
• በወር አበባ ዑደት መካከል ከማህፀን ደም መፍሰስ
• የታችኛዉ የሆድ ክፍል ላይ ህመም/ቁርጠት መኖር
• የወር አበባ ዑደትዎን ማዛባት፡- የወር አበባ ዑደትዎ ከሚመጣበት ቀን ተጨማሪ ለአንድ ሳምንት መራዘም፡፡ የወር አበባ ዑደትዎ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብሉን በወሰዱ በ3ና 4 ሳምንታት ዉስጥ ካልመጣ የእርግዝና ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል/ ይመከራል፡፡
መቼ መወሰድ አለበት፡- የመከላከያ እንክብሉ የመከላከል ብቃቱ ብቁ እንዲሆን የመከላከያ እንክብሉን ግንኙነት ካደረጉ በኃላ ወዲያዉ መዉሰድ፤ ከ72 ሰዓታት ዉስጥ ግን መዉሰድ አለበት፡፡ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ እንክብል በወር አበባ ዑደቱ በየትኛዉም ጊዜ ሊወሰድ ይችላል፡፡

Comments

comments