ስለወር አበባ ዑደትዎ ትክክል የሆነዉና ያልሆነዉ ነገር ምንድን ነዉ?
የወር አበባዎን መከታተል ስለእርስዎ የወር አበባ ዑደት ትክክል የሆነዉን ለመረዳት፣እንቁላል ከአብራኳ የምትወጣበትን ጊዜ ለማወቅና ሌሎች አስፈላጊ ለዉጦችን ለመለየት ይጠቅምዎታል፡፡ ለምሳሌ የወር አበባ ዑደት መዘግየትን ለማወቅ ወይም ቀኑን ያልጠበቀ የወር አበባ መፍሰስ የመሳሰሉትን ለመከታተል ይረዳል፡፡ ምንም እንኳ የወር አበባ ዑደት መዛባት ሊከሰት የሚችል ነገር ቢሆንም አንዳንዴ የህመም ማሳያም ሊሆን ይችላል፡፡
ስለወር አበባ ዑደት ትክክል የሆነዉ/ኖርማል ነገር ምንድነዉ?
የወር አበባ ዑደት የሚቆጠረዉ መፍሰስ ከጀመረበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለዉ የወር አበባ ዑደት የመጀመሪያ ቀን ሲሆን ይህ ርዝማኔ በሁሉም ሴቶች ላይ አንድ አይነት አይደለም፡፡ ኖርማል የሚባለዉ የወር አበባ ዑደት በየ 21 እስከ 35 ቀን ባለዉጊዜ ዉስጥ የሚመጣ ሲሆን መፍሰሱ ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ማያት በጀመሩበት ጊዜያት/ዓመታት ያሉ የወር አበባ ዑደቶች ርዝማኔ አጫጭር ሲሆኑ እድሜዎ እየጨመረ ሲመጣ ግን እየተስተካከለ ይመጣል፡፡
እድሜዎ እየጨመረ መጥቶ ወደማረጥ ሲቃረቡ ደግሞ የወር አበባ ዑደቱ ተመልሶ እየተዛባ ሊመጣ ይችላል፡፡ እድሜዎ እየጨመረ ሲመጣ ለማህፀን ካንሰር የመጋለጥ እድሉ እየጨመረ ስለሚመጣ የወር አበባ መዛባት በዚህ ጊዜያት ካለዎ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡፡
የወር አበባ ዑደቱን እንዴት መከታተል ይቻላል?
የራስዎን የወር አበባ ዑደት ትክለኛዉን እርዝማኔ ለማወቅ የወር አበባ ዑደትዎን በካላንደር ላይ መመዝገብ ይጀምሩ፡፡ ይህም የወር አበባ ዑደቱ በትክክል መምጣቱንና አለመምጣቱን ለመከታተል እንዲረዳዎ የወር አበባ ዑደቱ መፍሰስ ከጀመረበት ቀን ጀምረዉ ለተከታታይ ወራት (ቢያንስ ለ6 ወራት) በየወሩ በመደዳ ይመዝግቡ፡፡
ስለሆነም ስለወር አበባ ዑደትዎ የሚያሳሰውብዎ ነገር ካለ በሚከተሉትን ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተዉ ይመዝግቡ
-
የመጨረሻ ቀን፡-
የወር አበባ ዑደቱ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ከተለመደዉ የዑደት እርዝማኔ ማጠር ወይም መርዘም አለዉ ወይ?
-
የአፈሳሰሱ ሁኔታ፡-
የወር አበባ ዑደቱ የአፈሳሰስ መጠን ከተለመደዉ በላይ ነዉ ወይስ በታች? የንፅህና መጠበቂያዉን በቀን ምን ያህል ጊዜ ይቀይራሉ? የረጋ ደም ይፈሳል ወይ?
-
ያልተለመዳ ከብልት ደም መፍሰስ ካለዎ፡-
በወር አበባ ዑደትዎ መሃል ከብልት ደም መፍሰስ አለዎ?
-
ህመም፡-
ከወር አበባ ዑደቱ ጋር ተያያዥነት ያለዉ ህመም አለዎ? ህመሙ ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ የተባባሰ ነዉ?
-
ሌሎች ለዉጦች ካሉ፡-
የባህሪይ ወይም ፀባይ/ሙድ/ መቀያየር ገጥሞታል? የወር አበባ ዑደት ለዉጥ በነበረበት ወቅት አዲስ የተቀየረ ነገር አለ?
የወር አበባ ዑደት ያለመስተካከልን/መለዋወጥን የሚያመጡ ነገሮች ምንድናቸዉ?
የወር አበባ ዑደት መለዋወጥን የሚያመጡ/ የሚያስከትሉ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም
-
እርግዝና/ጡት ማጥባት፡-
የወር አበባ ዑደት መዘግየት ካለ የእርግዝና ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከእርግዝና በኃላ ጡት ማጥባት የወር አበባ ዑደት ተመልሶ ሳይመጣ እንዲዘገይ ሊያደርግ ይችላል፡፡
-
ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም/ Polycystic ovary syndrome (PCOS)፡-
የዚህ የሆርሞን መዛባት ችግር ያላቸዉ ሴቶች ያልተስተካከለ የወር አበባ ዑደትና የእንቁሊጤ መጠን መጨመር ሊታይ ይችላል( የመጠን መጨመሩ እንቁሊጤዋ ዉሃ ስለምትቋጥር ነዉ፡፡
-
የዳሌ ዉስጥ መቆጥቆጥ /Pelvic inflammatory disease (PID)፡-
የመራቢያ አካላት ኢነፌክሽን ለዚህ አይነት ችግር ሊዳርግ ይችላል፡፡
-
የማህፀን ላይ እጢ፡-
የማህፀን ላይ እጢ ካለዎ የወር አበባ ዑደት መጠን መብዛትና መራዘም እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል፡፡
-
የተወሰኑ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች፡-
የወሊድ መከላከያ እንክብሎች፣ ሉፕና ሌሎችም የወር አበባ ዑደቱን ሊያዛቡ ይችላሉ፡፡
የወር አበባ ዑደት መዛባት እንዳይከሰት እንዴት መከላከል ይቻላል?
ለአንዳንድ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል መዉሰድ የወር አበባ ዑደቱ ተስተካክሎ እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የሚከተሉት ለዉጦች ካሉ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡
- እርግዝና ሳይኖር የወር አበባ ዑደትዎ ከ90 ቀናት በላይ መቋረጥ ካጋጠመዎ
- ተስተካክሎ ይመጣ የነበረዉ የወር አበባ ዑደት መዛባት ከጀመረ
- የወር አበባ ዑደት ከሰባት ቀናት በላይ መፍሰስ ካለዉ
- ከተለመደዉ መጠን በላይ የደም መፍሰስ ካለ ወይም በቀን ዉስጥ ከተለመደዉ ቁጥር በላይ የንፅህና መጠበቂ/የወር አበባ ደም መቀበያ ፓድ መቀያየር ካጋጠመዎ
- የወር አበባ ዑደት እርዝማኔዉ/የሚመጣበትገዜ/ በየወሩ ከ21 ቀናት በታች ካጠረ ወይም ከ35 ቀናት በላይ መዘግየት ካለዉ
- በወር አበባ ዑደት መካከል የደም መፍሰስ ካለዎ ናቸዉ፡፡
ማስታወስ የሚገባዎ ነገር ቢኖር ስለወር አበባ ዑደትዎ ማወቅ ስለእርስዎ የወር አበባ ዑደት ትክክለኛ የሆነዉንና ያልሆነዉን ለመለየት ይጠቅምዎታል፡፡ስለሆነም ከተለመደዉ ዉጪ ትክክል ያልሆነ ነገር ካለዎ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡፡
Related Posts
-
ልጅዎ የአምስት አመት እድሜ ሳለ
ከዚህ በፊት የህፃን ልጅዎን የአጨዋወት፣ አነጋገር/ ቋንቋ፣ እንዴት እንደሚማር እና እንቅስቃሴዎችን እንዴት እንደሚተገብር በመከታተል ስለልጅዎ…
-
የኢስትሮጂንና ፕሮጀስቲን የወሊድ መከላከያ እንክብሎች
የአጠቃቀም ሁኔታ፡- የወሊድ መከላከያ እንክብሎች አስተማማኝና የማይጎዱ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዴትና መቼ እንደሚወሰዱ እና ምን…
- ጉንፋን
ጉንፋን የላይኛው የመተንፈሻ አካልን (አፍንጫን፣ጉሮሮሮንና ሳንባን) የሚያጠቃ በቫይረስ ኢንፌክሽን አማካይነት የሚመጣ የህመም አይነት ነዉ፡፡ ከአምስት…