የኩላሊት ጠጠር

 

የኩላሊት ጠጠር በኩላሊትዎ ዉስጥ ትናንሽና ጠንካራ የሆኑ ማዕድናት ሲጠራቀሙ የሚመጣ ችግር ነዉ፡፡ ድንጋዮቹ የተሰሩት ከማዕድናትና አሲድነት ካላዉ ጨዉ ነዉ፡፡ የኩላሊት ጠጠር መነሻ መንስኤ ብዙ ሲሆኑ በየትኛዉም የሽንት መተላለፊያ መስመር ዉስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ብዙዉን ጊዜ የኩላሊት ጠጠሮች የሚከሰቱት ሽንት በሚወፍርበት/ concentrated/ በሚሆንበት ወቅት ሲሆን ይህ ማዕድናቱ እንዲረጉና እንዲጣበቁ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

የህመሙ ምልክቶች

በአብዛኛዉን ጊዜ የኩላሊት ጠጠሮች በኩላሊትዎ ዉስጥ ካልተዘዋወሩ አሊያም ወደ ዩሬተር(ሽንትን ከኩላሊትዎ ወደ ፊኛ የሚወስደዉ ቱቦ) ካልወረዱ በስተቀር ምንም አይነት የህመም ምልክት አያሳዩም፡፡ ስለሆነም የሚከተሉት የህመም ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡
• ጎንና ጀርባዎ ላይ ከፍተኛ ህመም መኖር
• ወደ ታችኛዉ የሆድዎ ክፍልና ብሽሽት የሚሰራጭ ህመም መፈጠር
• ሽንት ሲሸኑ ህመም መኖር
• ቀይ ወይም ቡናማ የመሰለ የሽንት መልክ መከሰት
• ጉም የመሰለ ወይም ሽታ ያለዉ ሽንት መዉጣት
• ማቅለሽለሽና ማስታወክ
• በተደጋጋሚ ለመሽናት መፈለግ
• ከተለመደዉ ጊዜ/ብዛት በላይ ሽንት መሽናት
• ኢንፌክሽን ካለ ትኩሳትና ብርድ ብርድ ማለት መኖርና
• በጣም ትንሽ መጠን ያለዉ ሽንት መሽናት ናቸዉ፡፡
በኩላሊት ጠጠር ምክንያት የሚከሰተዉ ህመም ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ጠጠሩ ወደ ሌላ ቦታ ከሄደ/ ከተዘዋወረ ህመሙ ሊጨምር የችላል፡፡


የህክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?


የሚከተሉት የህመም ምልክቶች ካሉ የህክምና ባለሙያዎን ባስቸኳይ ያማክሩ፡፡
• ህመሙ በጣም ከፍተኛ ከሆነና መቀመጥ ያለመቻል ወይም ምቾት የሚሳንዎ ከሆነ
• ህመሙን ተከትሎ ማቅለሽለሽና ትዉከት ከመጣ
• ከህመሙ ጋር ትኩሳትና ብርድ ብርድ ማለት ካለ
• ከሽንትዎ ጋር ደም ከመጣ
• ሽንትዎን መሽናት ከተቸገሩ


ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች


• በዚህ በፊት በቤተሰብዎ ወይም በራስዎ ላይ መሰል ችግር ከነበረ
• የፈሳሽ እጥረት/ ድርቀት ካለ፡- በየቀኑ ፈሰሽ በበቂ መጠን መዉሰድ ካልቻሉ ለኩላሊት ጠጠር ይጋለጣሉ፡፡ ከሌሎቹ ይልቅ በሞቃታማ የአየር ንብረት ዉስጥ የሚኖሩና ከመጠን ያለፈ ላብ የሚያልባቸዉ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡
• የተወሰኑ የምግብ አይነቶች፡- የፕሮቲን፣ የሶዲየምና የስኳር ይዘታቸዉ ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ለተወሰኑ የኩላሊት ጠጠር አይነቶች ይጋለጣሉ፡፡
• ዉፍረት፡- ከመጠን ያለፈ ክብደት ያላቸዉ ሰዎች ላይ የኩላሊት ጠጠር የመፈጠሩ ጉዳይ ከፍተኛ ነዉ፡፡


የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር መከላከል


የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥና መድሃኒቶች ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታሉ፡፡
• በየቀኑ በቂ ፈሳሽ/ዉሃ መጠጣት፡- ሞቃታማና ደረቅ የአየር ንብረት ዉስጥ የሚኖሩ ከሆነ ወይም በመደበኛ ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ሽንት በበቂ መጠን እንዲመረት/እንዲወጣ ፈሳሽ በበቂ መጠን መጠጣት ይመከራል፡፡ ሽንትዎ ነጣ ያለና ንፁህ ከሆነ ዉሃ በበቂ መጠን እየወሰዱ መሆኑን ያሳያል፡፡
• መጠነኛ የኦክዛሌት/ oxalate ይዘት ያላቸዉን የምግብ አይነቶች ማዘዉተር፡- የካልሲየም ኦግዛሌት ድንጋይ እየተፈጠረ ካለ ወይም ተጋላጭነት ካለዎ እንደ ስኳር ድንች፣ ቆስጣ፣ ኦቾሎኒ፣ ሻይ፣ ቼኮሌት፣ የአኩሪ አተር ተዋፅኦዎችና ቀይስር ያሉ ምግቦች መመገብ ያስፈልጋል፡፡
• የጨዉና የፕሮቲን ይዘታቸዉ አነስተኛ የሆኑ ምግቦችን መምረጥ/ማዘዉተር፡- የሚመገቡትን የጨዉ መጠን መመጠን እንዲሁም ከእንስሳት ተዋፅኦ ዉጪ ያሉ የፕሮቲን ምንጮችን መመገብ ( ለምሳሌ ባቄላና አተር)
• የካልሲየም ይዘታቸዉ ከፍ ያለ ወይም በካልሲያም የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ነገር ግን የካልሲየም ሰፕሊመንት(ተጨማሪ እንክብል) ሲወስዱ ጥንቃቄ ያድርጉ፡- በካልሲየም የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ የኩላሊት ጠጠር የመፈጠር እድሉን አይጨምሩትም፡፡ የህክምና ባለሙያዎ ካልከለከለዎ በስተቀር የካልሲየም ይዘታቸዉ ከፍ ያሉ ምግቦችን መመገብ ይቀጥሉ፡፡ ነገር ግን የካልሲየም ሰፕልመንቶች ከኩላሊት ጠጠር መከሰት ጋር ተያያዥት/ግንኙነት ስላላቸዉ ከመዉሰድዎ በፊት የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡፡

Recent Posts

Comments

comments