ቴታነስ ከፍ ያለ የጤና ችግር ሊያመጣ የሚችል በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ፣ በተለምዶ መንጋጋ ቆልፍ የሚባል የህመም አይነት ነዉ፡፡ ሕመሙ ሲከሰት በአዕምሮ ነርቮች ላይ፣ህመም ያለዉ የጡንቻ መኮማተር በተለይ በመንጋጋና በአንገት ጡንቻዎች ላይ እንዲከሰት ያደርጋል፡
የህመሙ ምልክቶች፡-
የቴታነስ የህመም ምልክቶች የቴታነስ ባክቴሪያ ቁስል ላይ እንፌክሽን በተከሰተ ከጥቂት ቀናት አንስቶ በሳምንታት ዉስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ የህመሙ ምልክቶች እንደ አመጣጡ ቅደም ተከተላቸዉ ሲታይ
• በመንጋጋ ጡንቻዎች ላይ የመኮማተርና የመድረቅ/የመቆለፍ ስሜት መከሰት
• የአንገት ጡንቻዎች መገተር
• የመዋጥ ችግር
• የሆድ ጡንቻዎች መጠንከር/መድረቅ
• ለብዙ ደቂቃዎች የሚቆይ ህመም ያለዉ የሰዉነት መኮማተር፤ ታማሚዉ ያለበት ክፍል ሆኖ ከፍ ባለ ድምጽ ማዉራት፣የታማሚዉ አካል በእጅ ሲነካ፣ ክፍሉ ብርሃን ሲሆን የመሳሰሉት የሰዉነት መኮማተርን ያባብሳሉ/እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡
ሌሎች የህመሙ ምልክቶች
• ትኩሳት
• ሰዉነትን ማላብ
• የደም ግፊት መጨመር
• የልብ ትርታ መጨመር
የህመሙ መንስኤ
የቴታነስ ህመም የሚመጣዉ ክሎስትሪዲየም ቴታኒ በሚባል ባክቴሪያ ሲሆን ባክቴሪያዉ በአፈር፣ በአቧራ/ቡናኝና የእንስሳት አይነምድር ዉስጥ ይገኛል፡፡ባክቴሪያዉ ቁስል ባለበት ቦታ በሚገባበት ወቅት እዚያ ቦታ በማደግና ቶክሲኖችን ወደ ነርቮች በመልቀቅ ነርቮችን ስራቸዉን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደርጋል፡፡
ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች
• ክትባት ጭራሹኑ ያልተከተቡ ወይም በበቂ መጠን ያልወሰዱ ከሆነ
• የሰዉነት አካል ላይ አደጋዎች መከሰት፣ ሚስማር የመሳሰሉት
• አደጋ በደረሰበት አካባበቢ እብጠት መከሰት
ሊደረጉ የሚችሉ ምርመራዎች
ቴታነስን የህክምና ባለሙያዎች በአካላዊ ምርመራ፣ የህክምናና የክትባ ታሪክን በመጠየቅ፣ የጡንቻ ላይ ህመምና መወጠር የህመም ምልክቶች መኖርን በማየት ሊለዩ ይችላሉ፡፡ የላብራቶሪ ምርመራዎች ብዙም ላያግዙ ይችላሉ፡፡
የህመሙ ህክምናዎች፡-
ህክምናዉ የሚያጠቃልላቸዉ ነገርች ቴታነስ አንታይ ቶክሶይድ፣ፀረ-ባክቴሪያዎች፣የጡንቻ መወጠርን የሚቀንሱ መድሃኒቶች፣ ፀጥ ያለና ብርሃን በብዛት የማይገባበት ጨለማ ክፍል ዉስጥ ማቆየት፣ቁስል ካለ ቦታዉን መንከባከብና የመሳሰሉት ናቸዉ፡
እንዴት ሊንከላከለዉ እንችላለን
በአጠቃላይ ሲታይ ሁሉም በሚቻል ደረጃ ቴታነስ የተያዙ ሰዎች ክትባት ያልተከተቡ ስለሆኑ ቴታነስን ለመከላከል ክትባት መዉሰድ ብቻ ከህመሙ እራስን መከላከል ይቻላል፡፡
ለምክረዎ እጅግ እናመሰግናለን
Your Comment
በጣብ :አሪፍ ትምርት ነው ያገኘሁበት:አመስግናለው! በርቱ።
Very Good